Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጎንደር 61 ፕሮጀክቶች ማምረት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለሃብቶች መካከል 61 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታና ማምረት መሸጋገራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መመሪያ አስታወቀ፡፡

በከተማው በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 210 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡

የመምሪው ሃላፊ አቶ አዲሱ ደባልቄ እንደተናገሩት÷ በከተማው የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 11 የጨርቃጨርቅ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የኬሚካልና መሰል አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል ።

50 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን አቶ አዲሱ ጠቅሰው ወደ ማምረት የገቡትና በግንባታ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶችም ለ4 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በከተማው የተፈጠረው የተረጋጋ ሰላም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር አግዟል ብለዋል ሃላፊው፡፡

በከተማው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚውል 512 ሄክታር መሬትም ተዘጋጅቷል ።

በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ለረጅም አመታት አጥረው ያስቀመጡ ባለሀብቶችን በጥናት በመለየት 57 ባለሀብቶች የወሰዱት መሬት በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ እንዲሆን መደረጉንም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸውበቀጣይ ጎንደር የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን በጥናት በመመለስ የኢንዱስትሪ ከተማ እንድትሆን በጥብቅ እየተሰራ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version