አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሽታዬ መሃመድ እንደገለጹት÷ የምገባ አገልግሎቱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ እንዲከታተሉ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሸገር ከተማን ጨምሮ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 800 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ባለፉት 6 ወራት የተማሪዎች ዩኒፎርም እና የመማሪያ ግብዓት አቅርቦት የማሟላት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ ለማጠናከር ባለሃብቶችና አጋር አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ