አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት 4 ሺህ 392 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለአግባብ ለግለሰቦች እንዲሰጥ በማድረግና ይዞታውን በመውሰድ ከ132 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 48 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ የየካ ክ/ከ መሬት አስተዳደር የሰነድ አጣሪ የህግ ባለሙያ የነበረው አማረ ሞገስ፣ የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ የነበረው ቢኒያም ደነቀ እና የካሳ ኦፊሰር የነበረው ምስጋናው ማሰቦ ጨምሮ በ48 ግለሰቦች ላይ በ2015 ዓ.ም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ የየካ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሺዎችን እያስተያናገደ በነበረበት ወቅት ከ1ኛ እስከ 27ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሶች በክ/ከተዋም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ ሲሆን ከ28ኛ እስከ 36ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ደግሞ የአርሶ አደር ኮሚቴ ነን በሚል በወረዳ 10 እና ወረዳ 14 በተለያዩ ቦታዎች ከ37ኛ እስከ 48ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በአካባቢው ኗሪ ሳይሆኑ ኗሪ ናቸው በማለት ሀሰተኛ ቃለ ጉባኤ አቅርበዋል።
የክ/ከተማው ሰራተኛ ናቸው የተባሉት ተከሳሾች በህገወጥ መልኩ የካሳ ክፍያ እንዲዘጋጅ አድርገዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።
በዚህ መልኩ የልማት ተነሺ ላልሆኑ 10 ግለሰቦች የልማት ተነሺ ናቸው በሚል ለያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ይዞታ መብት እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ጠቅላላ ወቅታዊ የጨረታ ዋጋው 132 ሚሊየን 37 ሺህ 460 ብር ከ82 ሳንቲም የሆነ 4 ሺህ 392 ካሬ ሜትር ይዞታዎችን በህገወጥ መንገድ በምትክነት እንዲወሰድ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
ከተከሳሾች መካከል 11 ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን ቀሪ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደረገላቸው የጋዜጣ ጥሪ ባለመቅረባቸው እስኪያዙ ድረስ በሌሉበት ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቷል።
ችሎት የቀረቡና ክሱ የደረሳቸው ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃል በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 4ኛ፣ 6ኛ፣ 7ኛ፣ 8ኛ፣ 10ኛ፣ 16ኛ፣ 17ኛ፣ 18ኛ እና 20ኛ ተከሳሾች የተከሰሱበትን ድንጋጌ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 113(2) መሰረት በመቀየር በወንጀል ህግ 32 (1) ሀ፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) (ሀ) ስር ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ስር እንዲከላከሉ በማለት በወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ 142 (1) መሰረት ብይን ሰጥቷል፡፡
ቀሪ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ የተከሰሱበትን ድንጋጌ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 113 (2) መሰረት በመቀየር በወንጀል ህግ 32 (1) ሀ፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሀ) ስር ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው በማለት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 163/3 መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።
ከዚህም በኋላ 11 ተከሳሾች እንዲከላከሉ በተሰጠ ብይን መሰረት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቅሶ ጥፋተኛ ያላቸው ፍርድ ቤቱ፤ ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ