አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወሊሶ ከተማ ለሚገነባው ልዩ አደሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ብቁ፣ ተወዳዳሪና ለወደፊት ለሀገሪቱ ጠንካራ መሪ ለማውጣት ግብዓት የተሟላላቸው አዳሪ ት/ቤቶችን መገንባት ወሳኝ ነው፡፡
የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የት/ቤቱ ግንባታ በተያዘው ዓመት ተጠናቅቆ ከመላ ሀገሪቱ ከ8ኛ ክፍል በጣም ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩባት መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ለልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ ቦታ በማዘጋጀትና የግንባታ ወጪን በመሸፈን ላደረገው ድጋፍ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ አዳሪ ት/ቤቱ ከመላ ኢትዮጵያ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የልዩ አዳሪ ት/ቤቱ በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን 250 ተማሪዎች በመቀበል ሥራ እንደሚጀመር መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡