አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሌ ዒሳ ማህበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ “ሔር ኢሴ” የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ጅቡቲን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና ወንድማማችነት እንደሚያጠናክር ተገልጿል፡፡
“ሔር ኢሴ” በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር በድሬዳዋ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሚካኤል ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በእውቅና መርሐ ግብርሩ የተለያዩ ሁነቶችን ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
መርሐ ግብሩ የሔር ኢሴ ባህላዊ እሴትን የጋራ በማድረግ ለቱሪስት መስህብነት መጠቀምና ለቀጣይት ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ሔር ኢሴ የሶስቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንደሚያጠናክር ገልጸው÷ የአብሮነት፣ የወንድማማችነት፣ የሰላምና የመቻቻል ባህልን እንደሚያዳብር አውስተዋል፡፡
በመርሐ ግበሩ የሚታደሙ የሶማሊያ እና ጅቡቲ የስራ ሃላፊዎች ልዑካን ቡድን አባላት ድሬዳዋ መግባት መጀመራቸውን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በነገው ዕለት በሔር ኢሴ ላይ ለረጅም ዓመታት የተለያየ ጥናታዊ ጽሑፍ ባደረጉ ምሁራን ስለ ቅርሱ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
የፊታችን ቅዳሜ ደግሞ 30 ሺህ ሰዎች በሚገኙበት ቅርሱ እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የእውቅና መርሐ ግብር እንደሚከናወን ጠቅሰዋል፡፡
“ሔር ኢሴ” የሶማሌ ዒሳ ማህበረሰብ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ላለፉት 500 አመታት ሲጠቀምበት የኖረ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ ሲሆን÷ በዋናነት ይቅርታና የተጎዳን መካስ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ባህላዊ የእርቅ ስርዓት ነው፡፡
በመላኩ ገድፍ