አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አግሪ ውል ከተሰኘና የበጊዜ ኦፕቲማክስ እህት ኩባንያ ከሆነ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን ለማሳካት በሁሉም ዘርፍ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ጠንካራ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
በስምምነቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 1 ሚሊየን የግብርና ኮንትራቶችን ዲጂታል በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ለመደገፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
ከዲጂታል ኢትዮጵያ ሀገራዊ ግቦች ጋር በማጣጣም የግብርናውን ዘርፍ ለመለወጥ ትልቅ እድል ያለው ስምምነት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎችን ለማጎልበትና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ሂደቶችን ለማመቻቸት እንዲሁም ዘመናዊ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ነው የተነሳው።
በስምምነቱ ላይ የአግሪ ውል መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሩባቤል ክበበ እንዳሉት ፥ አገልግሎቱ የኢትዮጵያ የግብርና ኮንትራት ህግንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ፍላጎቶች ጋር የተጣጣመ ለተጠቃሚ ምቹ የሆነ የዲጂታል የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ ያደረጋል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ኑሮን ለማሻሻልና የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የዘርፉን የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በተጀመረው በዚህ ስራ የግብርናውን ዘርፍ የዘመናዊ መረጃ ከማደራጀት ባለፈ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተጠቁሟል።