Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወባን ለማስወገድ አዳዲስ ስልቶችና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወባን ለማስወገድ አዳዲስ ስልቶች እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ÷ ስብሰባው የወባ መድሃኒቶችን ወጪ ለመቀነስ እና ወባን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስልቶች ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የወባ በሽታን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊነትና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም በመግለጽ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ተቋሞችን ማጠናከርና የመከላከል ስራዎችን ማጎልበት ከጥረታቸው ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት ለአጋር ድርጅቶች አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው÷ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭት ያሉ ምክንያቶች የበሽታውን ስርጭት እንዳባባሱት ጠቁመዋል።

ተጋላጭ የሆኑ እና ከጎረቤት ሀገር የሚገቡ ስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲሁም በልማት ኮሪደሮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየቱንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በየሳምንቱ የወባ ስርጭት የሚመለከት ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰው÷ በተሰራው የተቀናጀ ስራ ከወባ ጋር ተያይዞ የሚደርው ሞት ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።

የጌትስ ፋውንዴሽን የስትራቴጂ ኤንድ ካንትሪ ፓርትነርሺፕ ዳይሬክተር ብሩኖ ሙኔን ÷የፋውንዴሽኑ ስትራቴጂካዊ ግቦች ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ያለባቸውን ሀገራት ሸክም መቀነስ፣ የበሽታውን ማጥፋት ዘመቻ ማፋጠንና በሽታው መድሃኒት ከመቋቋሙ በፊት አስቀድሞ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

Exit mobile version