አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት መካከል የኢንተርኔት መለዋወጫ ነጥቦችን ተደራሽነት በማስፋት አዳዲስ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢጋድ የ2025 የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ ሲጠናቀቅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፤ ኮንፈረንሱ የቀጣናውን የኢንተርኔት የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታትና መፍትሄዎችን ለመተግበር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በአባል ሀገራቱ መካከል የኢንተርኔት መለዋወጫ ነጥቦችን ተደራሽነት ማስፋትና ሀብትና እና እውቀትን በመጠቀም አዳዲስ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
አባላቱ በጋራ ፖሊሲዎችንና ቴክኒካዊ ማዕቀፎችን ማውጣት ከድንበር በላይ በሆኑ የዲጂታል መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንቶችን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
እያንዳንዱን ማህበረሰብ የሚያንፀባርቅበት፣ ቀጣናውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፋና ሆኖ የሚታይበትን እና የላቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወቅቱ የሚሻውና ወደ ተግባር መግባት አስገዳጅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ በበኩላቸው፤ የኢጋድ አባል ሀገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገትን ማፋጠን እና የዲጂታል ገበያ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ድንበር ተሻጋሪ የእውቀት መጋራትን አቅም ለማጎልበት እና የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ መጠቆማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።