Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅርቦት የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ 36 በመቶ ደረሰ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅርቦት የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ 36 በመቶ መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ፋርማስቲካል ፎረምን ለማቋቋም ያለመ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅርቦት የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ 36 በመቶ መድረሱን ገልፀው፤ ይህም ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር የ28 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ የመድሀኒት ፍላጎቷን ለመሙላት በዓመት ከ21 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታወጣ አስታውሰዋል።

90 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የመድሀኒት አቅርቦት ከውጪ በሚመጡ ምርቶች የሚሸፈን መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ የመድሀኒት ምርት ድርሻ እንዲጠናከር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተደረገ የመንግስት አስቻይ የፖሊሲና መመሪያ ድጋፍ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት ድርሻ ቀድሞ ከነበረበት 8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የፋርማስቲካል ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር የሚያግዝ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር በማስፈለጉ ይህን ጉባዔ ማሰናዳት እንዳስፈለገም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለፁት።

በቃለአብ ግርማ

Exit mobile version