Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

2 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ለማሰጠት በሚል ከ8 ማሊየን ብር በላይ በማታለል የወሰዱ ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 2 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ለማሰጠት በሚል ከ8 ማሊየን ብር በላይ ከግለሰብ በማታለል ወስደዋል የተባሉ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል የተከሰሱትን ዘላለም አስራት እና ዘካሪያስ ሙላቱ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክ/ከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ውስጥ የፕላን፣ ትመና እና ምህንድስና ከፍተኛ ባለሙያ የነበረው ሄኖክ ዘሪሁን ደግሞ ነጻ ተብሏል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፤ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሚል ክስ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ በተጨማሪነት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ዝርዝር ክስ በ2016 ዓ.ም አቅርቦባቸው ነበር።

በክሱ፤ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ በግል ስራ የሚተዳደሩ ሆነው ሲሰሩ የማይገባቸዉን ብልፅግና ለራሳቸዉ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በቂርቆስ ክ/ከ ድሪም ላይን ሆቴል ውስጥ የናይል ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በ1991 ዓ.ም በክ/ከተማው ወረዳ 9 ቦሌ መንገድ ከሞቢል ነዳጅ ማደያ አጠገብ ለቢሮ አገልግሎት ግንባታ የሚሆን 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሰጠዉ በተወሰነ ጊዜ አለመረከቡን መነሻ በማድረግ 2ኛ ተከሳሽ ይህንን ጉዳይ ተከታትሎ የሚያስፈፅም ሰው አውቃለዉ በማለት 1ኛ ተከሳሽን በመጥራት ለድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተመስገን መሃሪ ያስተዋወቃቸው መሆኑ ተመላክቷል።

1ኛ ተከሳሽም ብዙ ሰዉ ስለማውቅ አስጨርሳለዉ በማለት ከድርጅቱ በመጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ውክልና በመውሰድ ለቂርቆስ ክ/ከ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ቀድሞ በተወሰነው መሰረት ይፈፀም የሚል በተቋሙ የማይታወቅ በሃሰት የተዘጋጀን ደብዳቤ ከከንቲባ ጽ/ቤት አስወስነናል በማለት ለግል ተበዳይ የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።

በግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በክ/ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ተመሳስሎ የተፃፈ ‘የሊዝ ውል እንዲዋዋሉ እና የሊዝ ክፍያ እንዲፈፅሙ” የሚል በተቋሙ የማይታወቅ በሃሰት የተዘጋጀ ደብዳቤ በማሳየት ቀርበዉ የሊዝ ውል እንዲዋዋሉ ለግል ተበዳዮቹ ገልጸው ሃሰተኛ የሊዝ ውል ፎርም በማዘጋጀት ውል ተቀባይ ቦታ ላይ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑት የግል ተበዳይን ስም ፅፈዉ እንዲፈርሙ በማድረግ፣ በውል ሰጪ ቦታ ላይ ደግሞ የተቋሙን ሃላፊ አስፈርመን ቀሪ የሊዝ ውል ትወስዳላቹ ክፍያዉን ክፍሉ በማለት የማታለል ወንጀል መፈጸማቸው በክሱ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ ለሊዝ የሚከፈል በሚል በንግድ ባንክ፣ በአዋሽና አቢሲንያ ባንክ በተለያዩ መጠኖች ገንዘብ ገቢ እንዲደረግላቸው እና በክፍለ ከተማዉ የማይታወቅ ሃሰተኛ ደረሰኝ የተወራረደ በማስመሰል ሃሰተኛ የገቢ ደረሰኝ ሰነድ ለግል ተበዳይ ተከሳሾች ከናይል ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ሥራ አስፈፃሚ 8 ሚሊየን 300 ሺህ ብር በማታለል የወሰዱ እና ገንዘቡንም ምንጩን ለመሸሸግ በተለያዩ ሰዎች ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ማስተላለፋቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይነት ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም ማስረጃውን መርምሮ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባባሉ ተጠቅሶ ከቀረበበት ክስ ነጻ ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመወሰን ለጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version