አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ ከተማ በ640 ሚሊየን ብር ወጪ በግል ባለሃብት የተገነባው ቀዳዴ ፋሚሊ ጀነራል ሆስፒታል ተመረቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሆስፒታሉ መገንባት ለምሥራቅ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ወደ መሀል ሀገር ሪፈር የሚደረጉ ኬዞችን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
የግል የጤና ዘርፍ አገልገሎት ሰጪ ተቋማትን ቁጥር በመጨመር ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ መሰል የግል ጤና ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸው አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።
ድሬዳዋን ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራም ሆስፒታሉ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡
የሆስፒታሉ ባለቤት አብዱረህማን አህመድ በበኩላቸው ለሆስፒታሉ ግንባታ 640 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰው÷ ለ264 ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ሆስፒታሉ የፀጉር ንቅለ ተከላ በመስጠት በምስራቅ ኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሆነም ተመላክቷል።
በያሲን ሸምሰዲን