Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋል ጀምረዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋል ጀምረዋል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

በዳውሮ ዞን የተገነባው የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል፡፡

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድሩ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡

ክልሉ በግብርና ልማት በስፋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፥ እምቅ የማዕድን ጸጋ የሚገኝበት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

እንደ ሀገር ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የቆዩ የከበሩ የማዕድን ጸጋዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋል ጀምራዋ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዛሬ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካም መንግሥት ጸጋን መለየት እና ሀብት መፍጠር ላይ ስኬታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የፋብሪካው መገንባት ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ጫናን የሚቀንስ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

Exit mobile version