አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በተያዘው ዓመት ተጠናቀው ሥራ እንደሚጀምሩ የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባውን የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካን መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ዛሬ የተመረቀውን ፋብሪካ ጨምሮ በዚህ ዓመት ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡ አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርቱን በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጪ ስታስገባ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም መስራት ሲጀምሩ በዓመት ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በተጨማሪ እስከ 400 ሺህ ቶን ትርፍ ማምረት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ዛሬ ተመርቆ ስራ የጀመረው ፋብሪካም በዓመት 450 ሺህ ቶን ያለቀለትና ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ማምረት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ይህም የሀገሪቱን 25 በመቶ የድንጋይ ከሰልን ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው የጠቆሙት፡፡
ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የመፍጨት አቅም እንዲኖረው የሚያስችል ማስፋፊያ እንደሚደረግለት የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ በፍቃዱ አሠፋ መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።