አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባለፈ ለቀጣናው ብልጽግና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንዳሉት÷የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ ለአፍሪካ ቀንድ እና አጎራባች ሀገራት ትብብር፣ የጋራ ብልፅግና፣ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ህዝቦች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ የጋራ ዕድገትንና ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር ጽኑ አቋሟን በተግባር እየገለጠች እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለአፍሪካ አንድነት እና ብልፅግና መሳካት የጋራ ተጠቃሚነት መርሕን በማስቀደም እየሰራች እንደምትገኝ ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን እያከናወነች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥በዚህም አዳዲስ ስብስቦችን እየተቀላቀለች ነው ብለዋል።
በዚህም ከእያንዳንዱ ጥምረት አባል ሀገራት ጋር የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ትብብሯን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲን እየተከተለች መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ለሕዝቧ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ይበጃሉ ብላ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ለኢዜ ተናግረዋል።
አምባሳደር ነብያት አያይዘውም ኢትዮጵያ ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰፊ ዝግጅት እያደረገች ነው ብለዋል።
ዝግጀቱ እንደ አስተናጋጅ ሀገር የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣትና እንደ አባል ሀገር ደግሞ በጉባኤው በንቃት የምትሳተፍባቸውና የምታንጸባርቃቸው አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።