Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ቲካሻ ቤንጊ” የጋራና አሰባሳቢ ትርክትን የሚያጎላ ነው-ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸኮ የዘመን መለወጫ በዓል “ቲካሻ ቤንጊ” በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸኮ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ነው።

 

“ቲካሻ ቤንጊ” የተዘራው እህል ደርሶ ከተሰበሰበ በኋላ በበጋው የፀሐይ ብርሃን ታጅቦ እህል በጋራ በመቅመስ የሚከበር በዓል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

 

ጠንካራ የሥራ ባህልን የሚያበረታታው “ቲካሻ ቤንጊ” በበዓሉ ዕለት ስለቀጣዩ አዝመራ እርሻ ሥራ የሚዘመትበት የደስታ በዓል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

 

የሸኮ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁስ አውደ ርዕይ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች የጭፈራ ትርዒትና የሸኮ፣ የቤንች፣ የሸካና የካፋ የባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት መሪ የሆኑ ምረቃ ከበዓሉ ኩነቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ነጋሽ ዋጌሾን (ዶ/ር ኢ/ር ) ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ እንዲሁም የቤንች ሸኮ ዞንና አጎራባች ዞኖች ተጋባዥ እንግዶች በበዓሉ ታድመዋል፡፡

 

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በዓሉ አብሮነት ፣አንድነትና ሰላም የሚገለፅባቸው ክዋኔዎችን መያዙ የጋራና አሰባሳቢ ትርክትን የሚያጎላ ነው ብለዋል።

 

በበዓሉ የታየውን አንድነት በልማቱ ዘርፍ መድገም እንደሚገባ ገልፀው ታላቅ ባህላዊ ዳራ ያለውን ይህን በዓል ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን÷ የአካባቢው ማህበረሰብ ከአጎራባች ህዘቦች ጋር በዓሉን በሰላምና በአንድነት ማክበር መቻሉ “ትካሻ ቤንጊ” ሰላምና አንድነት የሚሰብክና የሚያፀና በዓል ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

 

በተስፋዬ ምሬሳ

Exit mobile version