አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የላሊበላ መካነ-ቅርስ ላይ አጠቃላይ የጥገና ሥራ ለማከናወን በቅርቡ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊወጣ መሆኑን የቅርስ ባለስልጣን ገልጿል፡፡
የላሊበላ መካነ-ቅርስ ጥገና ዘላቂ ላሊበላ እንዲሁም አጠቃላይ የቅርስ ጥገና በሚሉ ሁለት ምዕራፎች መከፈሉን በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሃፍታሙ አብርሃ ተናግረዋል።
ለመጀመሪያው ምዕራፍ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን እንዲሁም ለሁለተኛው 5 ሚሊየን ዩሮ ወጪ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
ወጪው በፈረንሳይ መንግሥት እንደሚሸፈን ጠቁመው÷ አሁን ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ 24 በጣም አስቸኳይ እና አሳሳቢ ወይም የቅድሚያ ቅድሚያ ተብለው የተለዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሥራዎች ሁለተኛው ምዕራፍ እስከሚጀመር ቅርሱ ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ማቆያ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የምዕራፍ አንድ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱን እና የተሰነጠቁ አለቶችን የመሙላት፣ የተዘጉ የውኃ መፋሰሻ ቦዮችን የመክፈትና የማስተካከል፣ ለቅርሱ ብቻ ተብለው በስታንዳርዳንድ የተዘጋጁ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ማሟላትን ጨምሮ ለቅርስ ጥገናና ጥበቃ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሥጠት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
አጠቃላይ የጥገና ሥራውን ለመጀመርም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሣይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተጨማሪ ጥናቶች እንዲደረጉ መጠየቁን ተከትሎ÷ ሣይንሳዊ፣ ተአማኒ እና ተቀባይነት ያለው ተጨማሪ ጥልቅ ጥናት ለማድረግ እና ተያያዥ ሥራዎች ለማከናወን መታቀዱን አመልክተዋል።
ለዚህም በቅርቡ ዓለም አቀፍ ጨረታ ይወጣል ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው