Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጥራት ኦዲት መመሪያ እና ስታንዳርድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራት ኦዲት መመሪያ እና ስታንዳርዶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ኮራ ጡሽኔ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ÷ ተቋማት ለሚሰጡት ትምህርትና ስልጠና ጥራትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት።

በዚህም ቀጣይነት ያለውና እየተሻሻለ የሚሄድ የውስጥ ጥራት አጠባበቅ ስርዓት በመዘርጋት የትምህርት ጥራትን እንዲያስጠብቁ ሚኒስቴሩ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዜጎች የሀገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማሳለጥ የሚያስችል ዕውቀት፣ ክኅሎት እና አመለካከት ይዘው እንዲወጡ ከዘመኑ ጋር የሚስማማ የስልጠና ጥራት ኦዲት መመሪያ እና ስታንዳርዶችን አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅዋል።

ይህን ታሳቢ ያደረገ የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የጥራት ኦዲት መመሪያ እና ስታንዳርድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

የትምህርት ተቋማቱ በቀጣይ መመሪያው ከጸደቀ በኋላ በአዲሱ የስልጠና ጥራት ኦዲት መመሪያ እና ስታንዳርዶች መሠረት የሚመዘኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ከወዲሁ አዲሱን መመሪያ መሠረት አድርገው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

Exit mobile version