አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ፖሊስ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን (ስዋት) በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተዘጋጀው የፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ውድድር ለመሳተፍ ዱባይ ገብቷል፡፡
በፈረንጆቹ 2025 የፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ውድድር ቡድኑ ኢትዮጵያን በመወከል በታክቲካል ኦፕሬሽን ቻሌንጅ፣ በጥቃት፣ በቪአይፒ አመራር የማዳን ተልዕኮ፣ በከፍተኛ ማማ መውጣትና መውረድ እንዲሁም በመሰናክል ኮርስ ይወዳደራል ተብሏል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለቡድኑ ባደረጉት ሽኝት÷ ውድድሩ የኢትዮጵያ ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን ተሞክሮውን እንዲያከፍል እና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቡድኑ አባላት በውድድሩ ላይ መልካም ሥነ-ምግባር በማሳየት፣ በብቃት በመወዳደር እና በማሸነፍ የኢትዮጵያን እና የፌደራል ፖሊስ ተቋምን መልካም ገፅታ በዓለም መድረክ እንዲያስተዋውቁ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በውድድሩ አሜሪካና ቻይናን ጨምሮ ከ50 ሀገራት የተውጣጡ ከ120 በላይ ቡድኖች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡