Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ታጣቂዎች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በቡርቃ የተሃድሶ ማዕከል ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በክልሉ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች እንደነበሩ ተመለላክቷል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ታጣቂዎቹ የሕዝብን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሚል ወደ ጫካ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ጥያቄዎቹን ለማስመለስ የተከተልነው የትጥቅ ትግል አማራጭ የተሳሳተ ነበር ብለዋል፡፡

በትጥቅ ትግሉ የመጀመሪያ ተጎጂ የክልሉ ሕዝብ መሆኑን በመረዳታቸው ወደ ሰላም አማራጭ ለመመለስ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

በስልጠና ቆይታቸው የሕዝብ ጥያቄ በትጥቅ ትግል እንደማይመለስ መገንዘባቸውን ጠቅሰው፤ እስከ ዛሬ የበደሉትን ማህበረሰብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን ነው የገለፁት፡፡

የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ደጀኔ ልመንህ÷ የመንግሥት እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ስልጠና ማዕከል እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስልጠናውን ያጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎች በቀጣይ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሰላም አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው÷ በጫካ የሚገኙ ሌሎች የታጠቁ ወገኖችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው ሰላምን መምረጥ የታላቅነት መገለጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላም መንገድን መርጠው ለሕዝብ እፎይታ እንዲሰሩ ማስገንዘባቸውን የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ አመላክቷል።

በተመሳሳይ በሰራባ የስልጠና ማዕከል የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 1 ሺህ 490 ታጣቂዎች ተመርቀዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት በደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ እና ቁሳዊ ውድመት መፀፀታቸውን ጠቅሰው፤ የማይገባ ዋጋ የከፈለው ህዝብ ሰላም እንዲያገኝ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን መናገራቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

Exit mobile version