Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀገራዊ ምክክር የጋራ አቅጣጫን እንዴት እንተልም?

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ ባለድርሻ አካላት መካከል ለተፈጠሩ አለመግባባቶች በመነጋገር መፍትሔ እንዲመጣ የሚያደርግ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡

ሂደቱ ተከናውኖ አመርቂ ውጤት ባስመዘገበባቸው ሀገራት ባለድርሻ አካላት በሀገራዊ ምክክር የጋራ አቅጣጫን በማበጀት አንኳር በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ሀገራዊ መግባባትን ይፈጥሉ፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ በተወካዮች አማካኝነት ሲሳተፉ የጋራ መንገዶችን በመመስረት ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ተግባራትን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡-

የጋራ እሴቶችን መፈለግ

በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ ዜጎች አንድ የሚያደርጓቸው እሴቶቻቸው ላይ ማተኮራቸው በሂደቱ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጉዞ ፍሬያማ ያደርገዋል፡፡

የሰው ልጆች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን ክብር፣ ፍትሕ እና አንዱ ለሌላው መኖር ለሀገር አንድነት አስፈላጊ መሆናቸውን በመረዳት፤ እነዚህንም እንደመርህ መከተል የጋራ አቅጣጫን ለመተለም በእጅጉ ያግዛል፡፡

ከተለያዩ አቋሞች ጀርባ ያሉ ፍላጎቶችን መረዳት

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ወደ ምክክር መድረኮች ሲመጡ የተለያዩ አቋሞችን ሊያንፀባርቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

አንዳንድ ጊዜም ጥቂት የማይባሉ ባለድርሻ አካላት በእጅጉ የሚራራቅ አቋም መያዛቸው መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን መንገድ ረዥም ያደርጉታል፡፡

ሆኖም ግን አፅዕኖት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እነዚህ አቋሞች መነሻቸው ያልተመለሱ እና ቁርሾን የፈጠሩ የረዥም ጊዜ ፍላጎቶች መሆናቸው ነው፡፡

በመሆኑም ይህን ማድረግ አንዳችን የሌላችንን ሕመሞች እና ፍላጎቶችን በመረዳት የጋራ አቅጣጫን ለመተለም ያግዛል፡፡

ለትንንሽ ስኬቶች ዕውቅና መስጠት

የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ረጅም እና የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚፈልጉ ከመሆናቸው አንፃር እጅግ በርካታ ጉዳዮች በሂደቱ ተነስተው ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡

ሆኖም ግን ሂደቱ የሚፈጥራቸውን ትንንሽ ስኬቶች አጉልቶ በማየት እና ከተገኙ ስኬቶች በመነሳት ትልልቅ እና ውስብስብ ችግሮችን መፍታት ሂደቱን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡

ይህም የጋራ አቅጣጫ ለመተለም የሚደረገውን ጥረት ያጠናክረዋል፡፡

Exit mobile version