አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁን በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን የቢሮው ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ 112 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ባስጠናው ጥናት መሠረት ይህ ገንዘብ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባትና መጠገን በተጨማሪ ተጓዳኝ የትምህርት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው ብለዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው