አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት 17 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶች መሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታውቋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት÷የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾችን አቅም ማጠናከር አስችሏል።
በዚህም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የጓንትና ስሪንጅ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የፋይናንስና የመጋዘን ስርዓቱን በማዘመን የዲጂታል ሥርዓት መተግበር መጀመሩንም ነው የገለጹት፡፡
መድሃኒቶችን ከአገልግሎቱ ወደጤና ተቋማት ለማድረስ የሚያስችሉ 53 መኪኖች ተገዝተው ለስርጭት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 14 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች በግዢ ወደመጋዘን መግባታቸውን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ 17 ቢሊየን ብር የሚገመት የወባና ማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባትና ሌሎች የጤና ፕሮግራም መድኃኒቶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
በማዕከላዊ መጋዘን 83 በመቶ የመድሃኒት ክምችት መኖሩን ጠቁመው÷ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች 8 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶች እንደተሰራጩ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡