አዲስ አበባ፣ ጥር 19 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በበርካታ ባለብዙ መድረኮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኢኖንሴባ ሎሲን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን÷ የሁለቱን ሀገራት የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ጌዲዮን (ዶ/ር) ÷ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ አፍሪካ ኀብረትን ጨምሮ በበርካታ ባለብዙ መድረኮች ላይም በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።
አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲ በበኩላቸው÷ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ገልፀው ፤ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ህብረት፣ በብሪክስ ማዕቀፍ እንዲሁም በሌሎች ዓለም ዓቀፍ መድረኮች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል ።
አምባሳደሯ በመጭው ወር ለሚካሄደው ለ38ተኛ የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬትም በትብብር እንደሚሰሩ ማስታወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።