Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐሰተኛ የብር ኖት በመገበያየት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ በሐሰተኛ የብር ኖት በመገበያየት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ በቱሉ ቦሎ ከተማ ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ሰለሞን ጌታቸው እና ደሳለኝ አንጋሱ የተባሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በሐሰተኛ የብር ኖት ግብይት ሲፈጽሙ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክቷል።

አንደኛ ተጠርጣሪ ሰለሞን ጌታቸው ሐሰተኛ ባለ 200 የብር ኖት 36 ሺህ እንዲሁም ባለ 100 የብር ኖት 6 ሺህ በአጠቃላይ 42 ሺህ ሀሰተኛ የብር ኖት እንደያዘ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ሁለተኛ ተጠርጣሪ ደሳለኝ አንጋሱ ደግሞ ሐሰተኛ ባለ 200 የብር ኖት 1 ሺህ እንዲሁም ባለ 100 የብር ኖት 200 እንደያዘ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ፤ ህብረተሰቡ ግብይት ሲፈጽም በሐሰተኛ የብር ኖት ማጭበርበር እንዳይፈጸምበት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፏል።

Exit mobile version