አዲስ አበባ፣ ጥር 19 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በ2016/17 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ እስካሁን 505 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር)፤ የእርሻ እና የሆርቲካልቸር ዘርፍ ምርት ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በ2016/17 መኸር 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ ከዚህም እስካሁን 505 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
በመኸሩ ከ608 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስታውሰው የእስካሁኑ ውጤትም ከዕቅድ በላይ ምርት እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ በመኸር፣ በመስኖና በበልግ ከስንዴ ልማት 340 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ነው የተናገሩት።
በ2017 የበጋ መስኖ ስንዴ 4 ነጥብ 27 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 173 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን 3 ነጥብ 41 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በእዚህም ከመኸሩ እስካሁን 101 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት መገኘቱን ጠቅሰው በሩዝ ምርትም 1 ነጥብ 65 ሄክታር መሬት ታርሶ 48 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በአትክትልና ፍራፍሬ ልማትም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ እየተገኘ መሆኑን ማስታውቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡