አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየተካሄደ ባለው 26ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል እየተሳተፉ ነው፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ በጉባኤው የፌዴራል ፖሊስ ልምድና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፖሊስ አዛዦች እንደሚያካፍሉ ተገልጿል።
ሽብርተኝነትን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ እንደሚመክሩም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።
በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት አንገብጋቢ በሆኑ የፀጥታ ተግዳሮቶች ላይ በመምከር፣ የጋራ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እና እየተፈጠሩ ያሉ ተለዋዋጭ የወንጀል ድርጊቶች ላይ በመምከር ችግሮቹን ለመቅረፍ የትብብር ማዕቀፎችን የሚያጠናክሩበት ወሳኝ መድረክ እንደሆነም ይጠበቃል።