Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፓርቲው አቅጣጫዎች የድሬዳዋ የንግድ ማዕከልነትን ለማረጋገጥ እያስቻለ ነው – ከንቲባ ከድር ጁሃር

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የቀየሳቸው አቅጣጫዎች የድሬዳዋን የኢንዱስትሪ እና የንግድ ማዕከልነት እያረጋገጠ መሆኑን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

ከንቲባው ብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባዔ የቀየሳቸውን አቅጣጫዎች ተከትሎ በድሬዳዋ የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ውጤቶችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ፓርቲው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ድሬዳዋን የምስራቅ የሀገራችን ክፍል የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል እያደረገ ነው ብለዋል።

ሁሉም መሠረተ ልማቶች የተሟላለት የኢንዱስትሪ መንደር በመፈጠሩ በርካታ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ስራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን አንስተዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለሃብቶችን የካፒታል፣ የአገልግሎት፣ የመሠረተ ልማት እና የፋይናንስ ችግሮች ማቃለል በመቻሉ የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎችም ተኪ ምርት በማምረት እና ምርቶችን በጥራትና በብዛት ወደ ውጭ በመላክ ምንዛሪ በማስገኘት እንዲሁም በርካታ የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የገጠርና የከተማ መንገድ፣ የጤና እንዲሁም የትምህርት መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በመፍታትና አዳዲስ የማምረቻ ሼዶችን በመገንባት መሠረታዊ መፍትሄ ማምጣት መቻሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአረንጓዴ አሻራ እና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ በከተማ ግብርና እንዲሁም በአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ስራዎች ምርታማነት እንዲጨምርና ዋጋ እንዲረጋጋ ማድረጉን አንስተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የድሬዳዋ አስተዳደርን ዘላቂ ሰላም፣ የህዝቦችን ፍቅርና አንድነት ለመመለስ እንደ ሀገር በአብነት የሚጠቀስ ስራ መስራቱን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በቀጣይ ከተማዋን በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የላቀ ውጤት እንድታስመዘግብ ያስችላታል ብለዋል።

 

Exit mobile version