አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርአን እና አዛን ውድድር ሽልማት ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
ውድድሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነት በዘይድ አብን ሳቢት የቁርአን ማኅበር ነው፡፡
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ ውድድሩ ብቁ የቁርአን እና አዛን አንባቢዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ውድድሩ ሴት የቁርአን አንባቢዎችን በማሳተፉ በአፍሪካ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡
ከ60 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ታዳጊዎች፣ ሴቶች፣ ወጣት ተወዳዳሪዎች እንዲሁም የልዑካን ቡድን አባላት በውድድሩ እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡
ውድድሩ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።
በቅድስት አባተ