Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአገው ሕዝብ የሀገሩን ክብር፣ አንድነትና ማኅበራዊ ማንነት በጀግንነት አጽንቶ ኖሯል – አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአገው ሕዝብ የሀገሩን ክብር፣ አንድነት እና ማኅበራዊ ማንነነት በሁለንተናዊ ጀግንነት አጽንቶ የኖረ ነው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡

85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን” በሚል መሪ ሃሳብ በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ሃይል አሳፍረው በመመለስ የመንፈስ ብርታት አውርሰውናል ብለዋል።

ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ፈረሶችን እና ፈረሰኞችን ለመዘከር የአገው ፈረሰኞች በዓል በየዓመቱ እንደሚዘከር ገልጸዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል የተከፈለው መስዋዕትነት እና የጀግንነት ዋጋ በትውልዱ እንዲታሰብ የሚያደርግ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ፈረስ ከአገው ሕዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው አውስተው÷ የአገው ሕዝብ የሀገሩን ክብር፣ አንድነት እና ማኅበራዊ ማንነት በሁለንተናዊ ጀግንነት አጽንቶ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር ተባብረው የኢትዮጵያን ነጻነት እንዳስከበሩት ሁሉ እኛም የዚህ ዘመን ትውልዶች የአባቶቻችንን መስዋዕትነት በማስታወስ የሚጠበቀውን የብሔራዊነት ግዳጅ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስትር ዴዔታው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Exit mobile version