አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ከብሪክስ አባል ሀገር እህት ፓርቲ የሩሲያው ዩናይትድ ላዕላይ ም/ቤት አባል፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተርና የሴኔቱ ውጭ ጉዳዮች ም/ሃላፊ አንድሬይ ክሊሞቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች እና በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ÷ በፓርቲው አመራርነት ኢትዮጵያ በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ እና በተለያዩ ዘርፎች ፈጣን እድገት ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ በኩል ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በምታደርጋቸው ጥረቶች ጉልህ ሚና እያበረከተች መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በባለፉት ዓመታት ሕዝብን በማስተባበርና በማሳተፍ የተተከሉ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን በማጠናከር ሚናዋን የበለጠ እንድትወጣ እድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
አንድሬይ ክሊሞቭ በበኩላቸው÷ በ2ኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ ላይ እዲሳተፉ በመጋበዛቸው አመስግነው÷ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ወገኖች በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በዲፕሎማሲ መስክ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ÷በአቅም ግንባታ መስክ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም ተመላክቷል፡፡