አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በውጤታማነት በመፈፀም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞ እንድናፋጥን ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አሳሰቡ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወቃል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ በድምቀትና ዓላማውን ባሳካ መልኩ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
“ለፓርቲያችንም ሆነ ለሀገራችን በሚመጥን ከፍ ያለ ደረጃ የተዘጋጀው ይህ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ አካላት በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ”ሲሉም ገልጸዋል።
ጉባዔው በአንደኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም በጥልቀት የተገመገሙበት፣ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የተሻሻለበት፣ በአሰራር መሰረት ነፃ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ የአመራር አካላት የተመረጠበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የእስከአሁኑን ስኬቶችና ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደነበርም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ስለሆነም “በጉባዔው የተቀመጡትን አቅጣጫዎች በውጤታማነት በመፈፀም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞ እንድናፋጥን ሁላችንም በቁርጠኝነት እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉ አሳስበዋል።