Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ከቪዛ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማሃዲ ከሀገሪቱ የዜግነት፣ፓስፖርትና ኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ሳይመን ማጁር ፓቤክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ወቅታዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ነቢል÷በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቪዛና መኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን ችግር አስረድተዋል፡፡

በዚህም ዜጎች ላይ ጫና እየተፈጠረ መሆኑን አንስተው÷ ችግሩ እንዲቀረፍና ወጥ የሆነ አሰራር እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።

ሳይመን ማጁር ፓቤክ በበኩላቸው÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር የኢትዮጵያ መንግስት ለሰጠው ትኩረትና ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የቪዛና የመኖሪያ ፍቃድ አሰጣጥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር ለመፍታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ተቋማቸው በጀመረው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች ኤምባሲው ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በውይይቱ በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቪዛ፣ መኖሪያ ፈቃድና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚገጥሟቸውን ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version