አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅሩ በከፈለው መስዋዕትነት የክልሉን ሰላም በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል መቻሉን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ሰላምና የጸጥታ ቢሮ እና የተጠሪ የተቋማትን የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የአፈጻጸሙን ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር )÷ የጸጥታ መዋቅሩ በክልሉ ሕግን ለማስከበር ከፍተኛ ሥራ መስራቱን አስረድተዋል፡፡
የጸጥታ ኀይሉ በከፈለው መስዋዕትነት የክልሉን ሰላም በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል።
የጸጥታ መሪዎች ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ጽፈዋል ያሉት ም/ሃላፊው ÷የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ትግል ውስጥ በጀግንነት በመታገል ለሕዝብ ሰላም ሠርተዋል ብለዋል።
የጸጥታ ሃይሉ በክልሉ የነበረውን አስቸጋሪ የጸጥታ ችግር እና አካሄድ መቀልበሱንም አስገንዝበዋል፡፡
የታጣቂ ቡድኑን አቅም የማሳጣት እና ከጥቅም ውጭ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ጠቁመው÷ የአካባቢውን ሰላም በራሱ አቅም የመምራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁኔታውን የመቀልበስ፣ የማረጋጋት ፣ የማጽናት፣ እግር የመትከል እና የምሉዕነት ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል።
የታጣቂ ቡድኑን የመረጃ ምንጭ ማድረቅ እና እርምጃ የመውሰድ ሥራ መሠራቱንም ገልጸው÷ ክልሉ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።
የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ ከተሠሩ መልካም ሥራዎች ጎን ለጎን ችግሮች እንደነበሩም ነው ያስረዱት፡፡
ለሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ የማወያየት ክፍተቶች እንደነበሩም ተናግረዋል።
በራስ አቅም የአካባቢውን ጸጥታ ከማስጠበቅ ይልቅ ሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲመጡለት የመፈለግ አዝማሚያ ያለባቸው አካባቢዎችም አሉ ብለዋል።
የታጣቂ ኃይሉ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እንደ ሽፋን በመውሰድ የአማራን ሕዝብ አጎሳቁሏል ነው ያሉት። ለአማራ ሕዝብ እቆረቆራለሁ እያለ ከአማራ ሕዝብ ጠላቶች ጋር እየሠራ ነው ብለዋል። አማራን ከጠላቶቹ ጋር ሆኖ የሚወጋ ሃይል መሆኑንም ገልጸዋል።
ታጣቂ ሃይሉ የማድረግ አቅሙ መድከሙን እና መዋጋት ከማይችልበት አቅም ላይ መድረሱንም ጠቁመው÷ ታጣቂ ሃይሉ የክልሉ ሕዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይገባ እና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመራ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
መንታ መንገድ ላይ የቆሙ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው÷ ይህ አካሄድ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እንቅፋት እንደሚሆን ነው ያመላከቱት።
በጸጥታ ችግር ውስጥም ሆነው በርካታ የጸጥታ ሃይል ማሰባሰባቸውን እና ሥልጠና መሥጠታቸውን እነዲሁም የሠለጠነው የጸጥታ ሃይል ታሪክ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጸጥታ ሃይሉን የማጠናከር እና ሃይሉን እየጨመሩ የመሄድ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ጠንካራ የጸጥታ ሃይል እንዲኖር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው÷የጸጥታ ሃይሉን ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም ለማስከበር የተሠራው ሥራ መልካም መሆኑን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው÷ ከዚህ በላይ በመሥራት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሰላም ዙሪያ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን እና ህብረተሰብን ማዕከል ያደረገ የወንጀል መከላከል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።