Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡

ፍኖተ ካርታውን ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን÷እስከ ፈረንጆቹ 2032 ድረስ እንደሚተገበር ተመላክቷል፡፡

ፍኖተ ካርታው ለአርሶና አርብቶ አደሮች ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና የበለጸገ ሥነ-ምህዳር የመፍጠር ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር÷) የግብርና ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ዲጂታላይዜሽን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል አርሶና አርብቶ አደር ለመፍጠር ትኩረት በማድረግ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው የግብርና ኢንተለጀንስ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ ዘመናዊ እርሻ፣ የገበያ ትስስርና የኤክስቴንሽን የምክር አገልግሎትን ጨምሮ 6 ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን ጉዳዮችን ተግባራዊ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በሰለሞን በየነ እና ማርታ ጌታቸው

Exit mobile version