አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር አቀፍ የመንገድ ጉባዔ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት÷ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን በምታደርገው የልማት ጉዞ የመንገድ ዘርፉ ጉልህ ድርሻ አለው።
መንግስት ለመንገድ ልማት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት ባለፉት 6 ዓመታት በርካታ ውጤት መመዝገቡን አንስተው÷በኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን ከነበረበት 126 ሺህ ኪሎ ሜትር 171 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በፌደራል ደረጃ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በኩል 10 ሺህ 692 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ 160 የመንገድ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትሯ÷51 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ሊያበረክቱ የሚችሉትን የፍጥነት መንገዶች ለማስፋፋት የተጀመረው ሥራ ከአዲስ አበባ ወደ ሁሉም አቅጣጫዎች በሚወጡ መንገዶች ላይ ተገቢውን ጥናት በማካሄድ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል።
በጉባዔው የዘርፉ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም በፌዴራል፣ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች እንደሚቀርብ ተመላክቷል፡፡
በተለይም የአዲሱ የገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም አጀማመር ላይ የነበሩት ጥንካሬዎችና ክፍተቶች አስመልክቶ ውይይት ይደረግባቸዋል ነው የተባለው።
በቤዛዊት ከበደ