አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ መልሶ ያገገመ 229 ሺህ ሄክታር መሬት ለተደራጁ አርሶ አደሮች መተላለፉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ።
በቢሮው የተፋሰስ ልማት ቡዱን መሪ ጠዓመ ገብረስላሴ እንደገለጹት÷በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የተጎዱ መሬቶች በተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዚህም ቀደም ሲል በተለያዩ ተፋሰሶች በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የለማ 229 ሺህ ሄክታር መሬት በማህበር ለተደራጁ 198 ሺህ አርሶ አደሮች እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸዋል።
የለሙ ተፋሰሶችን ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነፃ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ አርሶ አደሮች በቋሚነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣቸው መደረጉንም አስረድተዋል።
አርሶ አደሮቹ የለሙ ተፋሰሶቹን ከመንከባከብ ባለፈ በንብ ማነብና በእንስሳት መኖ ልማት ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት አቶ ጠዓመ፣ ልማቱን ለማጠናከርም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለቁም እንስሳት መግዣ የሚሆን 194 ሚሊየን ብር በተዘዋዋሪ ብድር ማቅረቡን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።