Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፌደራል ፖሊስ ስዋት ቡድን አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በዓለም አቀፉ ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ውድድር ሲሳተፍ የቆየው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስዋት ቡድን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚህ ወቅት÷እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስ ተቋም በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ስዋት ቻሌንጅ ውድድር ላይ መሳተፉ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዓለም አቀፍ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትን ለማዳበር ፋይዳው የላቀ መሆኑ ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላችን ልምድና ተሞክሮ እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ለሚደረገው ውድድር መሻሻል የሚገባቸውን በመለየት በተሻለ ብቃት መዘጋጀት እንድንችል ዕድል የፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስዋት ቡድን አባላት በበኩላቸው÷በውድድሩ ከሌሎች ሀገራት የስዋት ቡድን አበላት ጋር ልምምድ በማድረጋችን በመሰናክል ውድድር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስዋት ቡድን ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሰርተፊኬት የተበረከተለት ሲሆን÷በቀጣይ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፍ መጋበዙንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version