አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሔራዊ ፓርክ እና በደቡብ ጎንደር ዞን የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ የተከሰተው የእሳት አደጋ በህብረተሰቡ እና አጋር አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር ውሏል።
የወረሂመኖ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አንተነህ ተስፋዬ እንደተናገሩት ፥ ፓርክኩ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በለጋንቦ ወረዳ አዋሳኝ አካባ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የእሳት አደጋው መከሰቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የአካባቢው ህብረተሰብ እና የወረዳው የፀጥታ ኃይል በጋራ ባደረገው ርብርብ የእሳት አደጋውን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በፓርኩ የተከሰተው የእሳት አደጋ ምንም እንኳን በብዝሃ-ህይወት ሃብቶች ላይ የከፋ ጉዳት ባይደርስም በግምት ከ15 ሄክታር ያላነሰ ስፍራ በእሳት መቃጠሉን ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የጉና ተራራ ጥብቅ ደን ተወካይ አቶ ወንድምነው ባይነስ ÷ በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኘው የጉና ተራራ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ እስቴ እና ላይ ጋይንት ወረዳ ባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ምክንያቱ ያልታወቀ የእሳት አደጋ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የአካባቢው ማህበረሰብ እና የሁለቱ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች ለተከታታይ ሦስት ቀናት ባደረጉት ርብርብ የእሳት ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻሉን አብራርተዋል፡፡
የሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች እንዳሉት ፥ ማህበረሰቡ ብሔራዊ ፓርኮችን እና የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎችን ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ፋይዳ በመረዳት ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የአማራ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡