Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕብረቱን የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል – ብሔራዊ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

ጉባዔውን በስኬት ለማከናወን 35 ተቋማትን ይዞ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቂያ በተመለከተ በጋራ ማብራሪያ ሰጥቷል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

የዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ማረጋገጥ የሚችሉ ከ40 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን ማስተናገዷን ተናግረዋል።

ለ38ኛው የህብረቱ ጉባዔም ኢትዮጵያ እንደ አባልና አስተናጋጅ ሀገር ዝግጅቱ ግልጽ አካሄድ እንዲኖረው ማኑዋል ማዘጋጀቷን ነው ያብራሩት።

የመረጃ ክፍተት እንዳይፈጠር በእንግሊዘኛ፣ በዓረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰለጠኑ በጎ ፈቃደኛ ካዴቶችን በማሰልጠን ስምሪት እንዲወስዱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ለሆቴል፣ ለትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ተገቢውን ግንዛቤ መፈጠሩንም በመግለጽ የፌደራል እና የአዲስአበባ ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ የእንግዶችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የቴሌኮምና መሰል አገልግሎቶችን በቅልጥፍና መስጠት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በልዩ ሳሎን እና በመደበኛው ተርሚናል በቂ የሰው ሃይል እንደተመደ እና እንግዶች ቀልጣፋ የኢሚግሬሽንና የጉምሩክ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በኩልም ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

የቻርተር አውሮፕላን ይዘው ለሚመጡ እንግዶች የመደበኛውን በረራ በማያስተጓጉል መልኩ በቂ የአውሮፕላኖች ማቆያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

Exit mobile version