Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአቶ ሃምዛ ቦረና ወይም ሃምዛ  አዳነ መዝገብ የተካተቱ 9 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአቶ ሃምዛ ቦረና ወይም ሃምዛ  አዳነ መዝገብ የተካተቱ 9 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ከሰአት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ  1ኛ ሃምዛ ቦረና ወይም ሃምዛ አዳነ፣ያለም ወርቅ አሰፋ፣ ታምራት ሁሴን ፣ ሰበቃ ቃርቴ፣ ጌቱ ተረፈን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች  ሲሆን ስምንቱ የአቶ ጃዋር ዋና ጠባቂዎች ወይም አጃቢዎች ናቸው።

በፌዴራል የመጀመሪያ  ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ  ችሎት  ለሶስተኛ ጊዜ በቀረቡ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ÷ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው 11 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሰራውን የምርመራ ስራ አብራርቷል።

በዚህም ምርመራ በተጠርጣሪዎች ላይ የተያዘ መሳሪያ ምርመራ ማድረጉን፣ ተጨማሪ 10 የተከሳሽ 20 ደግሞ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን  መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

በዚህም በአንደኛ ተጠርጣሪ ሃምዛ አዳነ ወይም ሃምዛ ቦረና ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ብሄርን ከብሄር እና ከሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉትን ቅስቀሳ የሚያመላክት በቪዲዮ ምስል የተደገፈ ማስረጃ እንዳለው ለችሎቱ ገልጿል።

በተጨማሪም 1ኛ ተጠርጣሪ በኦሮሚያ በተለያዩ ቦታዎች የብሄርና የሃይማኖት ግጭት መቀስቀሳቸውን የሚያስረዳ ምስክር ማግኘቱን አስረድቷል።

ከ3ኛ እስከ 8ኛ ያሉ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ብቻ  14 ሰዎች እንዲሞቱ  ምክንያት መሆናቸውን በምስክር ተረጋግጧል ያለው መርማሪ ፖሊስ ÷ በአጠቃላይ ከ350 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት  መውደሙን ማስረጃ መሰብሰቡንም ገልጿል።

ከዚያም ባለፈ በተጠርጣሪዎች በተፈጸመ ወንጀል በቡራዩ  የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ሌሎች አራት ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጾ÷ በዚህም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን የህከምና ማስረጃ ህይወታቸው ያለፉትን ደግሞ የአስከሬን ምርመራ ውጤት የመቀበል ስራ እንደሚቀረው መርማሪ ፖሊስ  አብራርቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በሚሰጣቸው  ትዕዛዝ ከሰኔ 23 እና ከ24 ቀን 2012 ዓ.ም  ውጪ በተለያዩ ጊዜያት  በፈጸሙት ወንጀል ሌላ ግኝት አግኝተናል ያለ ሲሆን÷ ሌሎች በርካታ የሰውና የሰነድ ማስረጃ እስክናሰባስብ ተጨማሪ 14 ቀን ይፈቀድልን ሲል አመልክቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ እየተከናወነ ያለው ምርመራ ተገቢነት የሌለው ነው  የሚቀርበው ምክንያት ተጨማሪ ጊዜ የሚያሰጥ አይደለም፣በእጃቸው ተገኘ የተባለው መሳሪያ በየጊዜው የቁጥር ስህተት እየቀረበበት ነው ፖሊስ ግልጽ አይደለም የሚሉ በርካታ መቃወሚያዎችን አንስተዋል።

አራት ተጠርጣሪዎች በአካለም ሆነ በስልክ ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት ፍቃድን ማግኘት እንዳለቻሉ በድጋሚ አቤቱታ አቅርበዋል።

1ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሃምዛ በበኩላቸው÷ እኔ  አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሆኜ በውጭ ሃገር ስኖር  የነበረና ለውጥ መጣ መባሉን ሰምቼ ወደሃገር የመጣሁ ሲሆን÷ በተለያዩ መገናኛና ብዙሃን ህገ መንግስታዊ መብቴን ተጠቅሜ የራሴን ያመንኩበትን ነው የገለጽኩት ሲሉ  ለችሎቱ ተናግረዋል።

መርማሪ  ፖሊስም ምርመራው የተፋጠነ  ፍትህ የማግኘት መብታቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን በመግለጽ÷ ማንንም  አስሮ ለማቆየት ሳይሆን አጠቃላይ የተፈጸመ ወንጀል ላይ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብና ለመመርመር መሆኑን ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚያም ባለፈ ፍርድ ቤቱም የወንጀሉን  ውስብስብነትና ስፋት ከግምት አስገብቶ የጠየቅሁትን ተጨማሪ ጊዜ ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም  ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ተከታትሎ ትእዛዝ መፈጸሙን እንዲያቀርብ  በተጨማሪም 1ኛ ተጠርጣሪ ህጋዊ ውክልና የሚሰጡበትን ሂደት እንዲያመቻች ትእዛዝ ሰጥቷል።

ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ከተጠየቀው 14 ቀን ውስጥ 8 ቀን በመፍቀድ ለሃምሌ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ውጤቱን ለመጠባበቅ ተለዋጭ  ቀጠሮ ሰቷል።

በታሪክ አዱኛ

 

Exit mobile version