Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቦርዱ ህወሓትን ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አገደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማገዱን አስታወቀ፡፡

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ለህወሓት ባለፈው ነሐሴ ወር የምዝገባና ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ተሰጥቶት እንደነበር አንስቷል፡፡

ፓርቲው ከተመዘገበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጠቅላላ ጉባኤውን ማድረግ፣ የፓርቲው አመራሮችን ማስመረጥ እንዲሁም ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማድረጉ አስቀድሞ ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ ይጠበቅበት እንደነበር ቦርዱ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርቲው ከላይ የተደነገጉ የቦርዱ መመሪያዎችን ሳይፈፅም በህግ የተሰጠው የስድስት ወር የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁበዚህም  ፓርቲው ለሶስት ወራት ምንም አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ መታገዱን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ፓርቲውን ያገደበት ዝርዝር መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ( ህ.ወ.ሓ.ት) ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን ለማሳወቅ የተሰጠ መግለጫ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ( ህ.ወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ያሻሻለውን ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 መውጣቱን ተከትሎ ህ.ወ.ሓ.ት ለቦርዱ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር 3944/ማኮ1/644 በጻፈውና ከዚሁ ደብዳቤ ጋር አያይዞ ባቀረበው ዝርዝር ሠነዶች፤ እንዲሁም የኢ.ፌ.ድ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር ፍሚ1/1345 በጻፈው ደብዳቤ መነሻነት ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ ለህ.ወ.ሓ.ት ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የክልላዊ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

ምዝገባውን ተከትሎ ፓርቲው ሊከተለውና ሊፈጽመው ስለሚገባው ህጋዊ ግዴታዎች ቦርዱ ነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15180 በተጻፈ ደብዳቤ ለፓርቲው ገልጿል።

ፓርቲውም የምዝገባ ሰርትፊኬቱንና የተጻፈውን ደብዳቤ ከቦርዱ ተቀብሏል።

ፓርቲው በዐዋጁና በመመሪያው መሠረት ከተጣለበት ኃላፊነትና ግዴታዎች መካከል ዋናዎቹ በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንሥቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ፤ በዚህም ጉባዔ ሠነዶቹን ከዐዋጁ ጋር አጣጥሞ ማጽደቅ፤ አመራሮቹን ማስመረጥ ፤ በተጨማሪም የቅድመ ጉባዔውን ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት የጉባዔውን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ ናቸው።

ፓርቲው በአዋጁና በመመሪያው መሠረት ያለበትን ግዴታዎች እንዲወጣ ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ይህውም ነሀሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15181፣ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15199 ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15209፣ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15278 በተጻፉ ደብዳቤዎች ያሳሰበና ያስታወቀ ሲሆን፤ በመጨረሻም ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15349 በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔ የማድረጊያ ጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ እንደቀረው በመግለጽ ፓርቲው በሕግ የተጣለበትን ግዴታ እንዲፈጽም በማሳሰብ ፓርቲው ይህንን የሕግ ግዴታ በወቅቱ ሳይፈጽም ቢቀር ቦርዱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሣኔ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል።

ይሁንና ፓርቲው የዐዋጁንና የመመሪያውን ድንጋጌዎችና የቦርዱን ውሣኔዎች በማክበር የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅና አመራሮቹን ሳይመርጥ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ ተጠናቅቋል።

ህ.ወ.ሓ.ትም በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ እንደሚንቀሳቀስ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሕግ፣ መመሪያና ውሣኔዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ሲገባው በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀፅ 3(11) (ሀ) እና ዐዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ አንቀጽ 16(6) የተደነገገውን ጥሦ ተገኝቷል።

በዚህ መሠረት ቦርዱ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ጉዳዩን መርምሮ ከዚህ የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥቷል፤

  1. ፓርቲው ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ዐዋጅና መመሪያ ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ባለማክበር ጉልህ ጥሠት በመፈጸሙ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016ን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀጽ 18(1) መሠረት ፓርቲው ይህ ውሣኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሣተፍ እንዲታገድ ቦርዱ ወሥኗል።
  2. ፓርቲው ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሠት በማረም፤ ዐዋጁን፣ ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ፣ የቦርዱን ውሣኔዎችና ትዕዛዞች በማክበር ፓርቲው ሊያደርግ የሚገባውን ጠቅላለ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችለውን የጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅና ቦርዱ ይህንኑ ሲያረጋግጥ በመመሪያው አንቀጽ 18(2) መሠረት ቦርዱ ዕግዱን የሚያነሣ መሆኑን ወሥኗል።
  3. ፓርቲው በተሰጠው የሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3(11)(ሐ) እና በመመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀጽ 19 (1) (ሐ) መሠረት ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ ቦርዱ ወሥኗል።
Exit mobile version