አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የመፍትሔ ሃሳቦች እንዲስተጋቡ ማድረጓን ትቀጥላለች ሲሉ የመስኖ እና ቆለማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ያሉትን ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉባኤዎች አስመልከተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን የማፍለቅና በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የመቃኘት ልምምዷን ወሳኝ መድረኮችን በማዘጋጀት ማስተጋባት ቀጥላለች ብለዋል።
ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ኮንፍረንስ 2025 የዚሁ ጅምር ጥረት አብነታዊ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በአጋርነት የተሳተፉበት እንደነበር ጠቅሰው፤ ከ13 ሀገራት የተወከሉ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ልኡካን አባላት በተቀመጡት አጀንዳዎች ላይ በስፋት መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮንፈረንሱ አፍሪካዊ አጀንዳዎችን በማቀንቀን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ኮንፈረንሱ በሚቀጥሉት ዓመታት በተሻለ ዝግጅት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡