አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሼክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ለዜጎች ጥራት ያለው ትምህርትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት፡፡
ትምህርትን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ÷ ለአብነትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻና በራሳቸው የሚያስቡ እንዲሆኑ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራቱ ግንኙነታቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአቅም ግንባታ፣ በነጻ የትምህርት እድልና በመምህራን ልምድ ልውውጥ የትብብር መስኮችን ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው÷ ቼክና ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፋይናንስ ድጋፍ ባሻገር በነጻ የትምህርት እድል፣ በመምህራን ልውውጥ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሳይንስ ዘርፎች ላይ የበለጠ ለመስራት ቀርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በነበራቸው ውይይት የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡