አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ውክልና ሥራን በአግባቡ በመወጣት ሕብረተሰቡ ለሚነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ አሳሰቡ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀጣይ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር የውክልና ሥራቸውን መስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ወ/ሮ ሎሚ በዶ በዚህ ወቅት÷በሕዝብ ውክልና ሥራ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታችና ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም አሰራሮችን በማሻሻል የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሀገር ደረጃ በሁሉም ዘርፎች ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመው÷ተቋማት ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ የም/ቤቱ አባላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ተመራጭ የምክር ቤት አባላት ከመረጧቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመነጋገር እና በመወያየት የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መንግስት አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራ ያለውን ሥራ ሕብረተሰቡ በመደገፍ የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትና የነበሩ ቁርሾዎችን ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው÷ይህን መልካም ዕድል በመጠቀም ከግብ ለማድረስ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እንዲሁም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ማለታቸውንም የም/ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡