አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህግ የበላይነት ማክበር፣ ማስከበር እና ፍትህን ማስፈን የህልውናችን መሰረት ነው ሲሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የህግ የበላይነት እና ፍትህ እንዲሰፍን ዘርፈ ብዙ ስራ እና ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲሰፍን በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እና ከህግ በታች መሆኑን ለማረጋገጥ በህግ የተጀመረው ስራ በህግ የሚጨረስ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል።
የተለያዩ ሃላፊነት የጎደላቸው እና ከእውነት የራቁ እንቅስቃሴዎች፣ ንግግሮች፣ መግለጫዎች በራስ ወዳድነት፣ ለግላዊ ጥቅም፣ ለርካሽ ተወዳጅነት እና ለዝና የሚደረጉ ድርጊቶች ለብዙ ጥፋት እና ጉዳት እንደሚዳርጉ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ሳቢያ የተፈጠረው ጊዜያዊ ረብሻ ማሳያ ሆኗልም ነው ያሉት።
ከአሁን በኋላም የህግ የበላይነትን የሚረጋገጠው እና ፍትህን ለማስፈን የሚተጋው እንደ አማራጭ ሳይሆን የሃገሪቱን እና የህዝቡን የህልውና ዋና መሰረት መሆኑን በመረዳት መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህጓ ተናግረዋል ።

