አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ የጋራ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ወደ ሁለቱም ተቋማት እንደሚመጡ አውስተዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ተመጋጋቢ ችግሮችን በጥልቀት በማየትና በመለየት በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው አንዱ የአንዱን በሕገ መንግስትና በአዋጅ ተለይተው የተሰጣቸውን ሚና በመረዳት የሚና መደበላለቅ ሳይፈጠር ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የጋራ ውሳኔ የሚሹ በርካታ አቤቱታዎች ወደ ተቋማቸው እንደሚመጡ ገልጻዋል፡፡
ሚኒስትሯ የጋራ ተግባራት በጥናት ተለይተው በቅንጅትና በትብብር ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ይመጣል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ ይህንኑ አሰራር ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ ስትራቴጂ እየተሰራ ሲሆን የስትራቴጂው ግንባታ በሕገ መንግስቱ ለሁለቱ ተቋማት የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባራት በአግባቡ እንዲያካትት ስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡
በዋናነት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ መወሰኑንም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ውይይቱ ሁለቱም ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶችን መነሻ በማድረግ የሚከሰቱት ጉዳቶችን ለመከላከልና አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

