አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣዩ አንድ ዓመት ቀሪ ተግባራትን በማጠናቀቅ አጀንዳዎችን የመቅረፅና ይፋ የማድረግ ስራ እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ያለፉት ሶስት ዓመታትን የስራ ክንውን እና የቀጣይ ዓመት ተግባራትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮሚሽኑ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ቀሪ ተግባራትን በማጠናቀቅ ምክክር ለማካሔድ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የዳያስፖራ አካላት ተሳታፊዎች ልየታ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው÷የምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎችን የማስወከል ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።
በዚህም በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጀንዳዎችን የመቅረፅና ይፋ የማድረግ እንዲሁም አማካሪዎችን እና አመቻቾችን የመለየት ስራ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡
ከሚካሔደው ምክክር የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን የማጠናቀርና ምክረ ሀሳቦችን የማቅረብ ስራ እንደሚከናወንም ነው የተናገሩት።
ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በማካሔድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡