Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መርማሪ ፖሊስ በአቶ ጃዋር መሃመድ ቤት በግለሰብ እጅ የማይገኙ ሳተላይቶችና ከውጭ በድብቅ የገቡ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል መርማሪ ፖሊስ በአቶ ጃዋር መሃመድ ቤት በድጋሚ ባደረገው ፍተሻ በግለሰብ እጅ የማይገኙ ሳተላይቶችና ከውጭ በድብቅ የገቡ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማግኘቱን ገለጸ።

መርማሪ ፖሊስ ሃምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በፍርድ ቤቱ በተሰጠው የ13 ቀን ተጨማሪ ጊዜ የሰራውን አዳዲስ የምርመራ ስራዎችን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በአቶ ጃዋር መሃመድ ቤት በድጋሚ በተደረገ ፍተሻ በግለሰብ እጅ የማይገኙ ሳተላይቶችና ከውጭ በድብቅ የገቡ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማግኘቱን አብራርቷል።

መሳሪያውንም ባለሙያ በድብቅ አስገብተው በማስገጠም በመሳሪያው የተለያዩ የታዋቂ ሰዎችን ስልክ በመጥለፍ ሲያዳምጡ እንደነበረ ማስረጃ ተሰብስቧል ብሏል መርማሪ ፖሊስ።

አቶ ጃዋር ሚዲያቸውን ተጠቅመው ብሄርን ከብሄር እንዲሁም የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ ባስተላለፉት ጥሪና ትዕዛዝ በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች 109 ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉ፣ 137 ላይ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ፣ 44 ሆቴሎች እና 328 የግል መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ 2 ሃውልቶች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸውን፣ 199 የንግድ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ላይም ጉዳት መድረሱን መርማሪ ፓሊስ ገልፆ በሌላ 26 የግል ተቋማት እና 53 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውንም ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

በተጨማሪም በቡራዩ የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 4 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሶ በቡራዩ ብቻ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያመላክት ማስረጃ መሰብሰቡን ይፋ አደርጓል።

ተጨማሪ የሰውና የሰንድ ማስረጃ ለማሰባሰብ 14 ቀን አንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የአቶ ጃዋር ጠበቆች በበኩላቸው ምርመራው ግልጽ ያልሆነና ደንበኛችንን አስሮ ለማቆየት የሚደረግ እና ፍርድ ቤቱን ተጽዕኖ ስር ለመክተት የሚደረግ ምርመራ ነው ሲሉ መቃወሚያ አንስተዋል።

ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉም ደንበኛቸው በዋስ እንዲወጡ የጠጠየየቁ ሲሆን፥ አቶ ጃዋርም በራሳቸው ተቃውሞ አሰምተዋል።

በቀዳሚነት እኛ የምንፈልገው የግል ሚዲያዎች ገብተው እንዲዘግቡ ነው፤ እየገቡ ያሉት የመንግስት ሚዲያዎች ናቸው ብለዋል።

እነሱም የመንግስትን ብቻ ነው የሚዘግቡት ስለዚህ ሌሎች እንዲገቡ ካልሆነም በአጠቃላይ እንዲከለከሉ ይደረግ ሲል አመልክቷል።

ፍርድቤቱም ነጻ ችሎት መሆኑን በመጥቀስ እስከአሁን ባለው ዘገባ የችሎቱን ውሎ እያቀረቡ መሆኑን በመጥቀስ በግል ደረጃም ለማዳመጥ ተሞክሯል ስህተት አልታየም ይሁንና በኛ ጉዳይ ዘገባ ተዛብቶብናል ካላችሁ አቤቱታ ማቀረብ ትችላላችሁ በማለት ስለሚዲያ አስተያየት አንቀበልም ሲል ችሎቱ አቶ ጃዋር ስለምርመራው ሃሳብ ብቻ እንዲሰጡ ጠይቋል።

አቶ ጃዋር መሃመድም የፖሊስ ምርመራ እኔን አይመለከትም፤ ይህ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ለፌዴራል ፖሊስ ምርማሪ ክብር አለኝ፤ በመንግስት ተመድቦልኝ ጥበቃ ሲደረግለኝ ነበር፤ መሳሪያውንም ሆነ አጃቤዎቼን መንግስት ነው ያቆመልኝ ይህ በውይይት የሚፈታ እንጂ አስሮ በመመርመር አደለም ብለዋል።

እኔ ለዚህ አገር ሰላም እየሰራሁ ነው፤ በምዕራብ እና በደቡብ ኦሮሚያ ከ1 ሺህ በላይ ታጣቂዎችን ከአባ ገዳዎች ጋር ሆኜ መሳሪያቸውን ለመንግስት ማስረከባቸውንም ተናግረዋል።

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተነሳውን ግጭት አስታርቄያለሁ፣ የሃይማኖት ግጭት አልቀሰቀስኩም ቤተሰቤም ሆኑ ከኔ ጋር የታሰሩት የኦርቶዶክስ እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸው።

ፍርድ ቤቱን ተጽዕኖ ስር ለመክተት ነው ብለው ላነሱት መቃወሚያም ፍርድ ቤቱ ነጻና ገልልተኛ የሆኑ ጉዳያቸውን እያየ መሆኑን በመጥቀስ እዚህ ቦታ የህግ ጉዳይ ብቻ ነው ሊነሳ የሚገባው ሲል አጽንኦት ሰቷል።

መርማሪ ፖሊስም የማንም ፖለቲካ አጀንዳ እንደማያስፈጽም እና በገለልተኝነት ምርመራውን እንደሚያደርግ ምላሽ ሰቷል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ተጠርጣሪው ፍርድ ቤቱን እንደዚህ አይነት ጥርጣሬ ወስጥ የሚከት ነገር እንዳያቀርቡ ትዕዛዝ ሰታል።

ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ በአቶ ጁሃር ላይ ተጨማሪ 12 ቀናት በመስጠት ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።

ዛሬ ፍርድ ቤት በቀረቡት በአቶ እስክንድር ነጋ ላይም ለተጨማሪ ምርመራ 9 ቀን ሰቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version