Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ 17ኛው የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአሶሳ ተከፈተ  

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጉሙሩክ ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ የከፈተው የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በይፋ ስታ ጀመረ።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የገቢዎች ሚንስትር አቶ ላቀ አያሌው እችና የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል?

በትናንትናው ዕለት በይፋ ሥራ የጀመረው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ 17ኛው የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ሆኖ መከፈቱ እንደተገለፀም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፥ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መከፈት የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት በህገ-ወጥ መንገድ በጥቂቶች እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከነበረበት አያያዝ ወጥቶ ወደ ተጨባጭ የሕዝቡ ጥቅም እንዲሸጋገር ያደርጋል ብለዋል።

የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ያግዛል ያሉት ኮሚሽነር ደበሌ፥ አስመጪና ላኪዎችም በህጋዊ መንገድ ተሠርቶ ማትረፍ እንደሚቻል አውቀው ሊሠሩ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ላቀ አያሌው፥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሁለቱ ሱዳኖች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የወጪና የገቢ ንግድ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ተናግረዋል።

የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መከፈትም የገቢና የወጪ ንግዱን ሚዛናዊ ለማድረግ እና ለባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የጉሙሩክ የሕግ ተገዢነትን ለማሳደግና የቀረጥና ታክስ ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥ ከዚህ ቀደም የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አለመኖር የክልሉ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት ከጎሮቤት ሱዳን ሀገር ጋር በንግዱ ዘርፍ ዘርፈ-ብዙ ሥዎችን በመሥራት እንዳይጠቀም አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።

የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መከፈትም ክልሉ በተለይም ከደቡብና ከሱዳን ጋር በወጪና ገቢ ንግዱ ዘርፍ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የአሶሳ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለ 8 ፎቅ የቢሮ ህንጻ ግንባታ እና የተለያዩ የጉሙሩክ መጋዘኖች ግንባታ የመሠረት ድንጋይም ተቀምጧል።

የገቢዎች ሚኒስትርና የጉሙሩክ ኮሚሽን በከልሉ በግጭትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማህበራዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ የሚሆን በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ግምታቸው 37 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሆኑ የምግድ ዘይት፣ ስኳር፣ አልባሳትና ጫማዎችን በድጋፍ አበርክቷል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version