አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮንሶና በአሌ አዋሳኝ ላይ ለተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሆኑ አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው ትናንት በሰጡት መግለጫ፥ ሰሞኑን በኮንሶ እና በአሌ ድንበር ላይ በተከሰተ የፀጥታ ችግር ምክንያት የ21 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል ብለዋል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እየሰራ ሲሆን፥ ለጸጥታው መደፍረስ ምክንያት የሆኑ አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
እስካሁንም በችግሩ ተሳታፊ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ 7 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ላይ ሲሆኑ፥ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ለዘመናት አብረው በኖሩ ህዝቦች መካከል አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሀይሎችን ሴራ ህብረተሰቡ ማጋለጥ አለበት ያሉት አቶ ርስቱ፥ የራሳቸውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በህዝቦች መካከል ቅራኔ ከሚፈጥሩ አካላት ራሱን እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአሁኑ ሰዓት አካባቢው በመረጋጋቱ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

